| 03.12.2008 | 14:00 UTC
ኒው ዴሊ፡ ኮንዶሊሳ ራይስ ህንድንና ፓኪስታንን ለማቀራረብ የጀመሩት ጥረት
በህንድና በፓኪስታን መካከል እየተጠናከረ የመጣውን ውጥረት ለማርገብ ዋሽንግተን በጀመረችው ጥረት መሰረት የዩኤስ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኮንዶሊሳ ራይስ ዛሬ ኒው ዴሊ ገቡ። ባለፈው ሳምንት በሙምባይ ከተጣሉትና ከአንድ መቶ ሰማንያ የሚበልጡ ሰዎችን ህይወት ካጠፉት ጥቃቶች ወዲህ የሁለቱ ጎረቤትና የኑክልየር ባለቤት ሀገሮች ግንኙነት እጅግ ሻክሮዋል። ህንድ የጥቃቱን ጠንሳሾችና አቀነባባሪዎችን ለመለየት በምታደርገው ምርመራ ላይ ፓኪስታን እንድትተባበራት ራይስ አሳስበዋል።
« ለፓኪስታን መንግስት መልዕክት አሰተላልፌያለሁ ። የፓኪስታን መንግስትም መልዕክቱን ተቀብሏል ። ወደ የትም ቢያመራን እነዚህ ሰዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ። በተጨማሪም መንግስቱ ተጨማሪ ጥቃቶችን ለመከላከል መረጃዎችን ለማሰባሰብ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ መሆናቸውን እርግጠኛ መሆን እንፈልጋለን »
ህንድ እንዳስታወቀችው፡ ከአጥቂዎቹ መካከል በህይወት የተያዘው አሸባሪ አጥቂዎቹ በጠቅላላ የፓኪስታን ዜጎች እንደነበሩና በዚያ እንደሰለጠኑ አረጋግጦዋል። የፓኪስታን ፕሬዚደንት አዚፍ አሊ ሳርዳሪ ህንድ ጥቃቱን በርግጥ የጣለው የፓኪስታን ቡድን መሆኑን ማስረጃ ካቀረበች፡ መንግስታቸው ርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
« የፓኪስታን ዴሞክራቲክ መንግስት በተዋናዮቹ ብሎም በጥቃቱ እጃቸው ባለበት ሁሉ ላይ ርምጃ ይወስዳል። » ይሁንና፡ ሳርዳሪ ሀገራቸው ለሙምባዩ ጥቃት በፍጹም ተጠያቂ አለመሆንዋን ነው ያመለከቱት።
« እንደሚመስለኝ፡ እነዚህ በካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሀገር የለሽ ተዋናዮች ናቸው። ጠመንጀኞቹና አቃጆቹ፡ ማንም ሆኑ ማን፡ መላ ዓለምን በዕገታ የያዙ ሀገር የለሽ ተዋናዮች ናቸው። የፓኪስታን መንግስት በፍጹም ኃላፊነት የለበትም፡ እንደማምነው። እንዲያውም፡ ኋይት ሀውስ እና የዩኤስ አሜሪካ ስለላ ድርጅት ፓኪስታን እጅዋ እንደሌለበት አስታውቀዋል። እኛ፡ የፓኪስታን መንግስት ከሰለባዎቹ መካከል ነን። ለህንዳውያኑ በጣም አዝናለሁ። »
ፓኪስታን ጥቃቱ በሚጣራበት ስራ ላይ ከህንድ ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆንዋን አስታውቃለች። ይህ በዚህ እንዳለ፡ የህንድ ባለስልጣናት በሙምባይ ላይ ጥቃት ሊጣል እንደሚችል ቀደም ሲል የቀረበላቸውን ማስጠንቀቂያ ችላ ማለታቸው በጋዜች ከወጣ ወዲህ የህዝቡ ቁጣ ገንፍሎዋል።




