| 29.07.2010 | 14:00 UTC
ኒው ዮርክ፡ የተመድ እና ንጹህ የመጠጥ ውኃ የማግኘት መብት
የተመድ ሁሉ ሰው ንጹህ የመጠጥ ውኃ የሚያገኝበትን መብት እንደ ሰብዓዊ መብት አውቆ ተቀበለ። ቦሊቭያ ያቀረበችውን እና ሰላሳ ሶስት ሀገሮች የደገፉትን ረቂቅ ውሳኔ አንድ መቶ ሀያ ሁለት የተመድ አባል ሀገሮች ሲደግፉት፡ አርባ አንድ ድምጽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። የተቃዋመ አልነበረም። ረቂቁን ውሳኔ ከደገፉት መካከል አንዷ የሆነችው የጀርመን የተመድ አምባሳደር ፔተር ቪቲግ ውሳኔውን ማለፊያ ሲሉ አሞግሰዋል።
« ጀርመን ሁሉም ንጹህ የመጠጥ ውኃ እና የመጸዳጃ አገልግሎት የሚያገኝበት መብት እንዲከበር ከሚጥሩት መካከል አንዷ ናት። ሁሉም ሰው ንጹህ የመጠጥ ውኃ እና እና የመጸዳጃ አገልግሎት ማግኘት አለበት የሚለውን ሀሳብ በኤኮኖሚ፡ በማህበራዊ እና በባህላዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ አስራ አንድ ላይ የተረጋገጠው መሰረታዊ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብት አካል አድርገን እናየዋለን። »
በዓለም አቀፍ ደረጃ 880 ሚልዮን ሰዎች ንጹህ የመጠጥ ውኃ አያገኙም። 2,5 ቢልዮን ደግሞ የመጸዳጃ አገልግሎት የላቸውም። በያመቱ ወደ አንድ ቢልዮን የሚጠጋ ሰው በቆሻሻ ውኃ ሰበብ በሚነሱ በሽታዎች ይሞታል።










